ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ከኮትዲቯር፣ ማዳጋስካርና ኒጀር ጋር ተደለደለች

ኢትዮጵያ አ ኤ አ በ2021 በካሜሮን ለሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያኮትዲቯርማዳጋስካርና ኒጀር ጋር ተደልድላለች። የማጣሪያ ድልድሉ ይፋ የሆነው በግብጽ ርዕሰ መዲና ካይሮ ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በተካሄደ የዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ነው።

48 ብሔራዊ ቡድኖችን በ12 ምድቦች ከፋፍሎ ከጥቅምት 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሚደረገው የማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ በምድብ 11 ከኮትዲቯር፣ ማዳጋስካርና ኒጀር ጋር ተደልድላለች።

ኢትዮጵያን ጨምሮ 44 ብሔራዊ ቡድኖች ቀጥታ ወደ ምድብ ድልድሉ የገቡ ሲሆን ሌሎች አራት ብሔራዊ ቡድኖች ወደ ምድብ ድልድሉ በቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የሚገቡ ይሆናል። ስምንት ብሔራዊ ቡድኖች የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የሚያደርጉት በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ መሰረት እንደሆነ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን አስታውቋል።

በዚሁ መሰረት ከመስከረም 27 እስከ ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም ላይቤሪያ ከቻድ፣ ደቡብ ሱዳን ከሲሺየልስ፣ ሞሪሽየስ ከሳኦቶሜና ፕሪንሲፔ እንዲሁም ጅቡቲ ከጋምቢያ የደርሶ መልስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በደርሶ መልስ ያሸነፉት አራት ብሔራዊ ቡድኖች የምድብ ድልድሉን ይቀላቀላሉ። በዚሁ መሰረት የላይቤሪያና የቻድ አሸናፊ በምድብ አንድ ከማሊ፣ ጊኒና ናሚቢያ ጋር የሚመደብ ሲሆን የደቡብ ሱዳንና ሲሸልስ አሸናፊ ቡርኪናፋሶ ኡጋንዳና ማላዊ በሚገኙበት ምድብ የሚደለደል ይሆናል። የሞሪሽየስ ከሳኦቶሜና ፕሪንሲፔ አሸናፊ በምድብ ሶስት ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካና ሱዳን ጋር የሚደለደል ሲሆን የጅቡቲ እና ጋምቢያ አሸናፊ ደግሞ በምድብ አራት ከዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ አልጄሪያና ጋቦን ጋር ይደለደላል።

ከምድብ ስድስት በስተቀር ከእያንዳንዱ ምድብ አንደኛና ሁለተኛ የሚወጡ አገራት ቀጥታ በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ይሳተፋሉ። በምድብ ስድስት ካሜሮን አዘጋጅ በመሆኗ በቀጥታ በውድድሩ የምትሳተፍ በመሆኑ በዚሁ ምድብ ከሚገኙት ኬፕቨርዴ፣ ሞዛምቢክና ሩዋንዳ አንዱ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ይሳተፋል።

ካሜሮን የ32ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ እንድታስተናግድ ተመርጣ የነበረ ቢሆንም በዝግጅት ማነስ ምክንያት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ የካሜሮን አስተናጋጅነትን በመንጠቅ ለግብጽ መስጠቱ የሚታወስ ነው።

በካሜሮን ለሚካሄደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ 12 ምድቦች

ምድብ 1 – ማሊ፣ ጊኒ፣ ናሚቢያ፣ ላይቤሪያ

ምድብ 2 – ቡርኪና ፋሶ፣ ኡጋንዳ፣ ማላዊ፣ ደቡብ ሱዳን/ሲሸልስ

ምድብ 3 – ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳን፣ ሞሪሸስ/ሳኦቶሜ

ምድብ 4 – ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ጋቦን፣ አንጎላ፣ ጅቡቲ/ጋምቢያ

ምድብ 5 – ሞሮኮ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ቡሩንዲ፣ ሞሪታንያ

ምድብ 6 – ካሜሩን፣ ሞዛምቢክ፣ ሩዋንዳ፣ ኬፕ ቨርዲ

ምድብ 7 – ግብፅ፣ ኬንያ፣ ቶጎ፣ ኮሞሮስ

ምድብ 8 – አልጄሪያ፣ ዚምባብዌ፣ ቦትስዋና፣ ዛምቢያ

ምድብ 9 – ሴኔጋል፣ ኮንጎ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ኢስዋቲኒ

ምድብ 10 – ቱኒዚያ፣ ሊቢያ፣ ታንዛኒያ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ

ምድብ 11 – አይቮሪኮስት፣ ኢትዮጵያ፣ ኒጀር፣ ማዳጋስካር

ምድብ 12 – ናይጄሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ቤኒን፣ ሌሶቶ

Share