17ኛው በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባሕል ፌስቲቫል ዝግጅት

እ.አ.አ.በ2002 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያውያን የስፖርት (እግር ኳስ)ና የባሕል  ዓመታዊ ውድድር በስዊስ የምጣኔ ሃብትና የፊፊ ዋና ከተማ በሆነችው ዙሪክ ውስጥ ሊጀመር ቀናቶች ይቀሩታል። ለ17ኛ ጊዜ ማለት ነው።

የእድሜውን ያህል እድገት አላሳየም እየተባለ የሚነገርበት ፌደሬሽን ላለፉት ዓመታት በርካታ ፈተናዎች አጋጥመውታል። በአውሮፓ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን (ትውልደ ኢትዮጵያውያንንም ያጠቃልላል) ቁጥር በየዓመቱ እያደገ ቢሄድም ውድድሮቹ እንዴት ብዙ ተሳታፊም ሆነ ተመልካች መሳብ አልቻሉም? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም።በዚህ ዓመት በአንደኛ ዲቪዝዮን 20 በሁለተኛ ዲቪዚዮን ደግም 16 ቡድኖች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፣ ከነዚህም መካከል 3  ቡድኖች ከአዲስ አበባ ይጠበቃሉ። በወጣቶች እንደተለመደው በሁለት የተከፈል የእስከ 12 እና 16 ዓመታት ሆነው ይፎካከራሉ።

በ2016 ሮም ላይ የነበረው ዝግጅት ብዙም እንዳልተዋጣለት ይታወቃል፣ ባለፈው ዓመት ሽቱትጋርት/ጀርመን ላይ በብዙ መልኩ የተበላሸና አዘጋጂዎቹንም ለኪሳራ የዳረገ ነበር።  

እኛም የራሳችንንም ምልከታ አክለን ሰዎች ምን ይላሉ እያልን አስተያየቶችን ስናቀርብ እንደነበረው ሁሉ የዘንድሮውስ ዝግጅት ምን ይመስላል? ብለን የኢትዮ ዙሪክ ቡድንና የአዘጋጅ ኮሚቴውን ሊቀመንበር የሆነውን አቶ ሙሉጌታ በየነ አነጋግረን ነበር።

 

ማረን ኃይለ ሥላሴ

የዘንድሮ ውድድር

ከዚህ በፊት ከነበሩት ውድድሮች ሁሉ ትምህርት የወሰደውና የዚህ ዓመቱ አዘጋጅ የሆነው የኢትዮ ዙሪክ ቡድን ተወዳዳሪ ቡድኖችን ብቻ ሳይሆን ጎብኝዎችንም የሚያስደስት ዝግጅት እየጠበቃቸው መሆኑን አቶ ሙሉጌታ  ይገልጻል።

ለዚህ ቃለ መጠይቅ በፈለግነው ጊዜ ውድድሩን አንዲመሩ ከተቀጠሩት ዳኞች ጋር ስብሰባ ላይ እንደነበር ነግሮኝ ዝግጅቱን በሚመለክት ረገድ ኢትዮ ዙሪክ ሙሉ በሙሉ እየተወጣው መሆኑንም በአጽንኦት ገልጾልኛል። ውድድሩም ስኬታማ አንዲሆን በማሰብ ዳኞች፣ የጸጥታ አስከባሪዎችና ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችም ሳይቀሩ ገንዘብ የተከፈላቸው  ፕሮፌሽናሎች መሆናቸውን አቶ ሙሉጌታ ይናገራል።’ በዚህ ዓመት ዋናው ትኩረት የሚሰጠው ለኳሱ ነው” የሚለው አቶ ሙሉጌታ፤ ሙዚቃን በሚመለክት አርብም ሆነ ቅዳሜ ተወዳጅ ሙዚቀኞች የሚታደሙበት ጥራቱ የተረጋገጠና ከኮንሰርቶቹ መጀመርያ በባለሙያዎች የሚታገዝ በቂ የጸጥታ ቁጥጥርም የሚኖረውና ካለፉት ዓመታት ሁሉ የተሳካ እንደሚሆን አቶ ሙሉጌታ በኩራት ይናገራል። ከላይ እንደተባለው ውድድሩን የሚመሩት ዳኞችን ጭምር አዘጋጅ ቡድን ብቻውን የሚመርጥና የሚዋዋል ከሆነ የፌደሬሽኑ ሚና ምንድነው? የቱላይ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ማጫሩ አይቀሬ ነው፤ አዎ ፌደሬሽኑ ቢያንስ በተወሰነ መልኩም ቢሆን በጋራ መሥራት ይጠበቅበት ነበር። በተለይ የቴክኒክ ኮሚቴው ተግባር ታድያ ምንድነው? የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ባለፈው ዓመት ሽቱትጋርት ጋር አዘጋጁ ቡድን መለመላቸው የተባሉ ዳኞች ያደረሱትን ጥፋት ያየን ሰዎች ፌደሬሽኑም ትምሕርት ቀስሞበታል ስለዚህም በቅንጅት ከአዘጋጅ ቡድን ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ይሠራል የሚለው ተስፋችን በዚህ ዓመት እውን እንዳልሆነ እያየን ነው።

የብዙ ሰዎች ስጋት የሆነውን የስዊዘርላንድ የኑሮ ውድነት አንስተንበት ማንም ቢሆን ምንም አይነት ስጋት ሊገባው እንደማይገባና አዘጋጅ ኮሚቴው እንዲያውም በአንዳንድ አገሮች ከነበረው ዋጋ ዝቅ ባለ ተመን እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን አቶ ሙሉጌታ አስምሮበታል።

አረፈ አይኔ ምትኩ

ተሳታፊ ቡድኖች

ወደ ተሳታፊ ቡድኖች ስንመለስ የወጣት ውድድሮችን ሳንጨምር  በአንደኛ ዲቪዚዮን  20 ቡድኖች በ4 ምድብ ተካተዋል፣ በ2ተኛ ዲቪዚዮን 16 ቡድኖች በ4 ተከፍለው ፕሮግራም ተይዞላቸዋል። በአንደኛ ዲቪዚዮን የአበበ ቢቂላና ኢትዮ ቡና ቡድኖች፣ በሁለተኛው ዲቪዚዮን ደግሞ ኢትዮ ሻላ ከኢትዮጵያ እንደሚመጡ ተነግሯል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱን በፌደሬሽኑ ጋባዥነት ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል። የጉብኝታቸው ዓላማም ለብሔራዊ ቡድን የሚመጥኑ ተጨዋቾች ካሉ ለመመልከት እንደሆነ ይታመናል። በነገራችን ላይ በስዊስ ሱፐር ሊግ ለዛናክስ ነሻቴል ተጨዋች የሆነው ማረን ኃይለ ሥላሴ  የሱፐር ሊግ ውድድር ስለተጀመረ እሱም ሆነ ወንድሙ ቅዱስ በዚህ ዓመት ውድድር ላይ አይኖሩም። በርካታ የስፖርት ጋዜጠኞች የቢቢሲ  የአማርኛ አገልግሎት የስፖርት ዘጋቢን ጨምሮ ለመምጣት አመልክተው ቪዛ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን የፌደሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዳንኤል ብስራት  አብራርቷል፣ በማከልም የዘንድሮው የክብር እንግዳ የቀድሞው የአካለ ጉዛይ በኋላ አምባሶይራ በመጨረሻውም ገደማ የመቻልና የብሔራዊ ቡድን ተጨዋች የነበረው አረፈ አይኔ ምትኩ ግብዣው ተልኮለት ቪዛ በመጠባበቅ ላይ መሆኑ ገልጿል አቶ ዳንኤል።

ጎብኚዎች ከአስተናጋጇ ከተማ ዙሪክ ምን ምን ይጠብቃሉ? ምንስ ሌሎች ከተሞች የሌላቸው ነገሮች ያገኛሉ?

ብዙ ሰዎች የስዊዘርላንድ ዋና ከተማ ጄኔቫ ይመስላቸዋል አንዳንዶች ደግሞ የለም ዙሪክ ነው የሚሉ አሉ። የስዊሶች ዋና ከተማ በመልክአ ምድር አቀማመጡ መሐል ላይ የሚገኘው በርን የሚባለው ከተማ ሲሆን ዙሪክ የምጣኔ ሃብት ዋና ከተማ ተብሎ ይታወቃል። ባንኮች፣ የመድህን (ኢንሹራንሶች)ና ታላላቅ የአካዳሚክ ተቋማት ያሏት ጥንታዊትም አዲስም ከተማ ነች ዙሪክ። ዝነኛው ባንሆፍ ሽትራሴና ፓራደ ፕላትዝ እጅግ በጣም ውድ የሆኑ አልባሳትና ጌጣጌጦች የሚሸጡባቸው፣ አንድ የእጅ ሰዓት እስከ 100ሺ ዶላር አንድ ባለ ጸጉር ካፖርት 70ሺ ዶላር የሴት ቦርሳ 30ሺ ዶላርና ከዚያም በላይ የሚያወጣባቸው ሱቆች ታገኛላችሁ በባንሆፍ ሽትራሴ አድርጋችሁ ፓራደ ፕላትዝ እስከተደርሱ ድረስ ብዙው ነገር ምርጥ ይሁን እንጂ ውድ ያልሆኑም ነገሮች አታጡም። ለዚህም ነው ዙሪክ ሁሉ የሞላብሽ የምትባለው።

የዓለም የእግር ኳስ ፌደሬሽን (FIFA) ዋናው መሥርያ ቤትም ያለው እዚሁ ዙሪክ ውስጥ ነው። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘመናዊ መልክ የተደራጀው የፊፋ ሙዝየም መጎብኘት ያለበት ቦታ ነው። ታላላቅ የትምሕርት ተቋማት እንደ ETH- Zürich እና ዙሪክ ዩኒቨርስቲም የሚገኙት እዚሁ ዙሪክ  ነው። በነገራችን ላይ ETH- Zürich ከ 1901 ጀምሮ 20 የሚሆኑ ጠቢባኖቹ የኖቤል ሽልማት ተሸላሚዎች ሲሆኑ ዙሪክ ዩኒቨርስቲም ዝነኛውን አልበርት አንስታይንን ጨምሮ 20 ተሸላሚዎች ያፈራ ታላቅ ተቋም ነው። ታላላቅ ሙዝየሞችና የጀልባ ሽርሽርም  ዙሪክ ከመጡ አይቀር መሞከር ያለበት ነው። በየከተማው ብትሄዱ የምታዩት ያው ከተማ ነው፤ ዙሪክ ስትመጡ ግን ከአልፕስ ተራራ እስከ ፊፋ ዋና መሥርያቤት ታገኛላችሁ፤ የስዊስ ፐርፌክሽን ከኢትዮጵያዊነት መስተንግዶ ጋር ይጠብቃችኋል፤ በሰላም ያገናኘን።

ዘገባውና ያዘጋጀው ምሥጢረ ኃይለ ሥላሴ

ፎቶ  ምሥጢረ ኃይለ ሥላሴ፤ በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን ስፖርትና የባሕልና ፌስቲቫል ድረ ገፅና ከአረፈ አይኔ ምትኩ ፌስቡክ ፔጅ የተወሰደ

Share