አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ የኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያዊው አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ በአሜሪካ ኒው ዮርክ ከተማ የተካሄደውን የኒው ዮርክ ማራቶን አሸናፊ መሆን ችሏል።

አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ ውድድሩን 2 ሰዓት ከ05 ደቂቃ ከ59 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመግባት ነው በአንደኝነት ያሸነፈው።

ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሹራ ቂጣታ ደግሞ 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃ ከ01 ሰከንድ በመግባት ውድድሩን ሁለተኝነት ማጠናቀቁ ተነግሯል።

ኬንያዊው አትሌት ጆፌሪ ካምሮው 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ በመግባት ውድድሩን በሶስተኝነት አጠናቋል።

በውድድሩ ላይ የተሳተፉ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ውስጥም አትሌት ታምራት ቶላ 4ኛ፣ አትሌት ታደሰ ያኢ 12ኛ፣ አትሌት ግርማ በቀለ 19ኛ እንዲሁም አትሌት ብርሃኑ ደሬ ከማል 20ኛ ደረጃን ይዘው በመግባት ውድድሩን አጠናቀዋል።

በሴቶች በተካሄደው የኒው ዮርክ ማራቶን ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ረሂማ ቱሳ 5ኛ፣ ማሚቱ ዳስካ 9ኛ እንዲሁም፣ በላይነሽ ፊቃዱ 10ኛ መውጣት ችለዋል።

በተመሳሳይ በሳምንቱ መጠናቀቂያ ላይ በተለያዩ የአለም ሀገራት በተካሄዱ በርካታ የጎዳናና ማራቶን ሩጫ ውድድሮች ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተካፋይ በመሆን ውጤታማነታቸውን ማሳየት ችለዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥም በፈረንሳይ ዴስ አልፕስ ማሪታይም ማራቶን በወንዶች ኢትዮጵያዊው አትሌት አብርሃም ሙላው 2 ሰዓት፣ ከ07 ደቂቃ፣ ከ50 ሰከንድ በመግባት ውድድሩን በአንደኝነት አጠናቋል።

ሴቶች በተደረገ ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ኑሪት ሽመልስ 2 ሰዓት ከ31 ደቂቃ ከ42 ሰከንድ በመግባት ውድድርን በአንደኝነት አጠናቃለች።

በደቡብ ኮሪያ ሴኡል ማራቶን ደግሞ በወንዶች ኢትዮጵያዊው አትለኬት አሰፋ መንግስቱ 2 ሰዓት ከ08 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ 1ኛ፣ አትሌት ታሪኩ ክንፉ 2 ሰዓት ከ08 ደቂቃ ከ19 ሰከንድ 2ኛ፣ አብደላ ጎበና 2 ሰዓት ከ08 ደቂቃ ከ32 ሰከንድ 3ኛ በመግባት ውድድሩን አጠናቀዋል።

ፖርቱጋል ፖርቶ ማራቶን ደግሞ በወንዶች ፍቃዱ ከበደ 3ኛ እንዲሁም አብርሃም ግርማ 5ኛ ደረጃን በመያዝ ሲያጠናቅቁ።

በሴቶች አትሌት አበባ ተከወሉ ገብረ መስቀል 1ኛ፣ አትሌት መስከረም አበራ ሁንዴ 2ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቀዋል።

በጃይና ሃንግዡ ማራቶን በሴቶች አትሌት ሂሩት ጥበቡ 1ኛ፣ አትሌት ፀሐይ ደሳለኝ 2ኛ እንዲሁም አትሌት ሲፈን መላኩ 3ኛ ደረጃን በመያዝ ውደድሩን አጠናቀዋል።

በጣሊያን ቶሪኖ በተካሄደው የማራቶን ውድድር ደግሞ በወንዶች አትሌት ሲራጅ ገና 1ኛ በመግባት ውድድሩን በአሸናፊነት ሲያጠናቅቅ፤ በሴቶች ደግሞ አትሌት ደንበሌ ጫፎ በተመሳሳይ 1ኛ ደረጃን በመያዝስ ውደድሩን በአሸናፊነት አጠናቃለች።

የዜና ምንጭ ፟  ፋና ብሮድካስቲንግ

Share