የክቡር ዶክተር አብይ የሥራ ጉብኝት በአውሮፓ

በምሥጢረ ኃ/ሥላሴ

ባለፉት 120 ዓመታት ውስጥ በታሪክ እንደተዘገበው የመጀመርያው ይፋ (ኦፊሲያል) ጉብኝት ያደረጉት ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን የቀዳማዊ  ኃይለ ሥላሴ አባት ልዑል ራስ መኮንን እ.አ.አ. በ1902 ዓ.ም. እንደሆኑ ይታመናል። የጉብኝታቸውም ዋና ዓላም የጃንሆይ እምዬ (ዓፄ) ምኒልክ እንደራሴ ሆነው በእንግሊዙ ንጉሥ ኤድዋርድ 7ተኛ የዘውድ በዓል ላይ ለመገኘት ሲሆን ፈረንሣይ ድል ያለ አቀባበል ተደርጎላቸው ፓሪስ ቆይተዋል። በሁለቱ ሀገራት ማካከል ብዙ ቁምነጎሮችንም ተዋውለው ፊርማዎቻቸውን አሳርፈዋል። ቀደም ሲል በአድዋው ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ በኢጣልያ ላይ ያስመዘገበችው ድል፣ በተለይም ራስ መኮንን ከድል አድራጊዎቹ የጦር መሪዎች እንደ አንዱና የአፄ ምኒልክ ልዩ እንደራሴ በመሆናቸው የተሰጠ ክብር ነበር።

ከሁለት አስርተ ዓመታት በኋላ በ1924 ዓ.ም የራስ መኮንን ልጅና የንግሥት ዘውዲቱ አልጋ ወራሽ ሆነው የተሰየሙት የዚያን ጊዜው ወጣት ራስ ተፈሪ መኮንንም አውሮፓን በይፋ ጎበኙ።  ቀደም ብሎ በ1923 ዓ.ም. ዋና መቀመጫው ጄኔቫ /ስዊዘርላንድ የሆነው የዓለም መንግሥታቱ ማሕበር  “ሊግ ኦፍ ኔሽንስ” ኢትዮጵያን አባል እንድትሆን አድርገው የነበሩት ራስ ተፈሪ መኮንን ያደረጓቸው ውሎችም ሆኑ ጉብኝታቸው ለየት ያለ ነበር።  በዚያን ዘመን አንድ የአፍርካ “መሪ” ወደ አውሮፓ ሲመጣ ቅኝ ገዢዎቹን ሊማጸን አልያም እጅ ሊነሳ እንጂ በእኩልነት ተቀምጦ ለመደራደር አልተለመደም ነበርና ወጣቱ አልጋ ወራሽ የብዙዎችን ትኩረት ሳቡ። በዘመኑም በቁጥር እጅግ በጣም ጥቂት የሆኑ ኢትዮጵያውያን በይበልጥ ለትምሕርት መጥተው ይኖሩ ስለነበር ከመሪያቸውና ተከታዮቻቸው ጋር ጠበብ ባለች እልፍኝ ተቀምጠው አኗኗራቸውን ጨምሮ በአገር ጉዳይ ላይ ሃሳብ ይለዋወጡ እንደንበርም ተነግሯል። ዘመን ተለዋውጦ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንደ ቀድሞው እድለኛ ትውልድ ለትምሕርት ወይም ሀገሩን ወክሎ ላባሕል ልውውጥ ሳይሆን ከሀገሩ ተገፍቶና ተሰዶ በተለያዩ ክፍላተ ዓለማት በተለይም አውሮፓ ይኖራል።  በተለይ ባሳላፍነው ሩብ ምዕት ዓመት ውስጥ የሀገራችን መሪዎች አይደሉም ተወካዮቻቸው አውሮፓ ዝር ቢሉና ሲሉ የሚጠብቃቸው ምን እንደነበር  የምናስታውሰው በጸጸት ነው።

 ክቡር ዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ በሚሰጧቸው ተስፋ፣ ፍቅርና ፍጹም ኢትዮጵያዊነት ብዙዎችን ማርከው የጥላቻ ግንብን አፍርሰው የፍቅር ድልድይ በመገንባት ላይ ይገኛሉ፤ እናንተም ተቋደሱ ብለው አውሮፓ ያለነውን ሁሉ ፍራንክፈርት/ ጀርመን ውስጥ የፊታችን ጥቅምት 21  (31.10.2018) ቀን ጋብዘውን ልንቀበላቸው፣ ልናገኛቸው፣ ልንጠይቃቸውና ሊመልሱልን ተቀጣጥረናል። “ኧረ ቀኑ አልደርስ አለን!” እየተባለ ነው ዛሬ የሚጠበቁት ክቡር ጠቅላይ ሚንስትራችን። ጠቅላይ ሚንስትሬ የምለው ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን እግዚአብሔር ይባርክ የሚል መሪ በሕይወት ዘመኔ በማግኜቴ ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ የማይል የለም። ‘’ቦ ጊዜ ለኩሉ’’ ለሁሉም ጊዜ አለው እያልን ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ በእኛነታችን ውስጥ ሰርጸዋል። እርግጥ ብዙ ገና ተቀባይነት ያላገኙ ስደተኞች ወገኖቻችን ስጋት አላቸው፤ ስጋታቸው የምንወደው መሪ መጣልን ስንል ከወደዳችሁትማ ለምን አብራችሁት አትሄዱም?  ቢሉንስ የሚለው ሚዛን የሚደፋ ስጋት ነው። ግን ለዚህም ቢሆን ገና ወደ ሥልጣን መጡ፣ ተስፋ ሆኑን እንጂ ሲዘራና ሲታጨድ ሲከመር፣ ሲንከባለል በተለይም ዘርን ከዘር የሚያባላው፣ የሚያፈናቅል፣ የሚያገዳድለው እኩይና መርዛማ ሥርአት ቶሎ እንደማይነቀል አስተናጋጅ ሀገራትም ሆኑ የዶክተር አብይ መንግሥት አሳምረው ያውቁታል ስለዚህም ይደራደሩበታል የሚል እምነት አለን። ስደተኛው ቢያንስም ቢበዛም ካለበት ሀገር ባለበት ሁኔታም ሆኖ ቤተሰቡን ብሎም ሀገሩን እየረዳ መሆኑን ተገንዝቦ  የዶክተር አብይ መንግሥት እውቅና ያላገኙ ስደተኞች ልዩ አስተያየት ተደርጎላቸው ሀገር እስኪረጋጋ ድረስ እየሰሩም ሆነ እየተማሩ እንዲቆዩ እንዲያደርጉላቸው፤ ያ ደግሞ ለኢትዮጵያ በገንዘብም ሆነ ቁሳቁስ እንደተደረገ እርዳታ ተደርጎ ሊቆጠር እንደሚችል አስምረው ሊነጋገሩበት ያስፈልጋል። ለዚህ ታሪካዊው የፍራንክፈርት ዝግጅት እየፈለጉ ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት መሄድ ያልቻሉ በሺዎች እንደሚቆጠሩ ዶክተር አብይ ሊይውቁትና ሊያስቡበት ይገባል።

ይህ በዚህ እንዳለ፣ የፍራንክፈርቱ አዘጋጅ ኮሚቴ በአውሮፓ ካሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዲያስፖራ ሀላፊዎች ጋር በመቀናጀት ለዝግጅቱ መሳካት ከፍ ያለ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ከአዘጋጅዎቹ አንዱ የሆነው ጋዜጠኛና አክቲቪስት ዘላለም ደበበ ይገለጻል። በየሀገራቱም፣ ኤምባሲዎች በሌሉባቸውም ጭምር ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው ተለያይቶ ሳይሆን ተባብሮና ተከባብሮ ሽር ጉድ በማለት ላይ ይገኛል። የይቅርታ ልቦና በጋራ ከሰማዬ ሰማያት የወረደ ይመስላል። አምላክ መጨረሻውም ያሳምረው

የሚጠየቅ መሪ ተገኝቶ ሕዝብ መሪውን ሊጠይቅ መሪውም ሊጠየቅ ሲገናኙ  በታሪካችን ውስጥ ከአፄ ምንሊክ ወዲህ ዶክተር አብይ የመጀመርያው እንደሆኑ ይታመናል። በቲማቲምና የገማ እንቁላል ሳይሆን በእቅፍ አበባና ቀና ልቦና ልንቀበላቸው የአውሮፓ ዲያስፖራውያን ቀን እየቆጠርን ነው።  በሰላም ይምጡልን ዶክተር አብይ።

ኢትዮጵያዊነት በክብር ለዘላለም ይኑር!!!

Share