ፈረሰኞቹን የሚያቆማቸው አልተገኘም

Kedus Giorgisየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አስራ ስድስተኛ ሳምንት አምስት ጨዋታዎች ባለፈው ማክሰኞ ተካሂደዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን ያጠናከረበትን ውጤት ሲያስመዘግብ ኢትዮጵያ ቡና ሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታውን በማሸነፍ ደረጃውን ከፍ እያደረገ መጥቷል።

የአስራ አንድ ጊዜ ሻምፒዮኖቹ ፈረሰኞች ተጨማሪ ዋንጫ ለማንሳት ግስጋሴያቸውን እያሳመሩ ይገኛሉ። በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር ሦስተኛ ጨዋታም የሚያቆማቸው ሳይገኝ ወደ ዋንጫው እየጋለቡ ይገኛሉ። ፈረሰኞቹ ኤሌክትሪክን በአዲስ አበባ ስቴዲየም ገጥመው ሦስት ለባዶ በሆነ ውጤት በመርታት መሪነታቸውን ሲያጠናክሩ ግቦቹን ከመረብ ማሳረፍ የቻሉት በመጀመሪያዎቹ ሠላሳ ደቂቃዎች ውስጥ ነው።

በመጀመሪያው የጨዋታ ጊዜ ፈጣን እንቅስቃሴ በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አስራ አራተኛው ደቂቃ ላይ ፊት አውራሪው አዳነ ግርማ በግንባሩ ገጭቶ የመጀመሪያዋን ግብ ከመረብ አዋህዷል። አዳነ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን ግቦች ዘጠኝ በማድረስም ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ለማጠናቀቅ መንገዶችን ማመቻቸት ችሏል። አይዛክ ኢዜንዴ በቅጣት ምት ሁለተኛውን ግብ ሲያስቆጥር አምና የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ሆኖ ያጠናቀቀው በኃይሉ አሰፋ ሦስተኛውን ግብ ከመረብ አሳርፏል።

ኢትዮጵያ ቡናን በሜዳው ያስተናገደው አዳማ ከተማ የአንድ ለባዶ ሽንፈት ደርሶበታል። በእዚህም ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ሰፍቷል። ያቡን ዊልያም በስልሳ አራተኛው ደቂቃ ቡናን ለድል ያበቃችውን ግብ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። በእዚህም በፕሪሚየር ሊጉ ከፈረሰኞቹ አጥቂ አዳነ ግርማ ጋር በእኩል ዘጠኝ ግቦች የኮከብ ግብ አግቢነቱን በሁለተኛነት መከተል ችሏል። ያቡን ዊሊያም በተከታታይ ጨዋታዎች ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ኢትዮጵያ ቡና በሁለተኛው ዙር ፕሪሚየር ሊግ ወጥ አቋም ያሳየና ደረጃውን ያሻሻለ ክለብ እንዲሆን ጉልህ ሚና ተጫውቷል። Read more Addis Zemen

Share

One thought on “ፈረሰኞቹን የሚያቆማቸው አልተገኘም

Comments are closed.