8ኛው የኢትዮጵያውያን የስፖርትና የባሕል ክብረ በዓል በአምስተርዳም ከተማ ሆላንድ ውስጥ 23 ቡድኖች ከተለያዩ የአውሮጳ ሀገሮችና ለመጀመርያ ጊዜ ከሰሜን አሜሪካም የሚሳተፉበት ውድድር 22/11/02 (28.7.2010) ይጀምራል:: በዚሁ ከአዋቆዎች የእግር ኳስ ውድድር በተጨማሪ የወጣቶች ውድድር በእግር ኳስና በሩጫም ይደረግበታል ተብሎ በሚጠበቀው ፕሮግራም ላይ በክብር እንግድነት የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች የነበረው ንጉሴ ገብሬና ድንቁ አትሌታችን ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴም የተጋበዙ ሲሆን በውድድር መነባበርና በጊዜ መጣበብ ምክንያት የኃይሌ መገኘት መቶ በመቶ የተረጋገጠ አይመስልም::
ይህ በእንዲህ እንዳለ አትሌት ኃይሌ የማይገኝ ከሆነ በምትኩ የቀድሞው ጀግናው አትሌት ሻምበል መሐመድ ከድር (የስዊዘርላንድ ነዋሪ) እንዲጋበዝ የሚጠይቁ አስተያየቶች ለፌደሬሽኑ እየቀረቡ መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል::ሻምበል መሐመድ ከድር “አረንጓዴው ጎርፍ” በሚል ስም የታወቀው የኢትዮጵያውያን ድንቅ አትሌቶች አባል የነበረና በተለይም እ.አ.አ. በ 1980 የሞስኮው ኦሎምፒክ ውድድር ላይ ሌላው ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጅ ምሩጽ ይፍጠር በ 5000 እና 10,000 ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች ለሀገሩ እንዲያስገኝ ከፍተኛውን የቡድን ሚና የተጫወተ መሆኑ አይዘነጋም::
ethiosports.com የውድድሩን ሂደት እየተከታተለ ለአንባቢዎቹ እንደሚያቀርብ ከወዲሁ በትህትና ይገልጻል::
ምሥጢረ ኃ.ሥላሴ
የ ሌዮኔ ደራሲ አጥናፍሰገድ ኪዳኔ በውድድሩ ሥፍራ ስለሚገኝ መጽሐፉን በ እጥረት ምክንያት ለመግዛት ያልቻላችሁ ሁሉ አሁን እዚያው ውድድሩ ላይ ለመግዛት ትችላላችሁ። ሌዮኔ በወንጀል፤ በፍቅር፤ በጀብድ፤ በፖለቲካና የሀገር ፍቅር ስሜት የተሞላ ድርሰት ሲሆን፤ ቁም ነገሩ ጥንታዊ የሆኑ የኢትዮጵያ ቅርሳ ቅርሶች ቀ.ኃ.ሥ. ከሥልጣን ከወደቁበት ጊዜ ጀምሮ በአንዳንድ ራስ ወዳድ ግለሰቦች እና ባለሥልጣናት እየተሰረቁ በአውሮፓ የጥንታዊ ዕቃዎች ገበያ ላይ እንደዋሉና እየዋሉ መሆኑ ላይ ነው።