(በአብዱልፈታህሲጋል)
በመጪዎቹ በርካታ የበጋ ሳምንታት ደጋግመን ከምንሰማቸው እግርኳስ ነክ ወሬዎች መካከል አውራው ስለ ፋብሪጋስ ወደባርሳ ዝውውርን በተመለከተ ይሆናል:: ግዥው ሳይንዛዛ ባጭሩ ሊጠናቀቅ የሚችልበት እድል ቢጠብም አለ:: ይህንን ጽሁፍም ሳዘጋጅ የካታላኑ ክለብ በ29 ሚልየን ፓውንድ ይፋ የሆነ የሽጡልኝ ጥያቄን አቅርቦ እንደተጠበቀው አርሰናሎች ውድቅ አርገውባቸዋል:: እንዲያው የፋብሪጋስ ዋጋ ያን ያህል ዝቅ ይላል ብሎ ማንም ባይገምትም የባርሳ ዋጋ ትመና ለድርድር መክፈቻ ያህል ለመሆኑ ግልጽ ነው:: ዋናው ማተኮር ያለብን ነገር ልጁ በግልጽ እንደተናገረው ወደ አሳዳጊው ክለብ መመለስ ይፈልጋል:: እንዲህ ያለ ቁርጥ ውሳኔ ላይ የደረሰን ተጨዋች ሞግቶ ማሳመን አሳምኖም እንዲቆይ ማድረግ ፋይዳ ቢስ መሆኑን በክርስትያኖ ሮናልዶ ዝውውር ሂደት የታየ በመሆኑ የአርሰናሎች ጥረትና ትኩረት በተቻለ መጠን ዋጋን ማናር ላይ እንደሚሆን ነው ::መጪው የውድድር ዘመን ፋብሪጋስ እንደተመኘው የባርሴሎናን ማልያ ቢያጠልቅ ተጫዋቹ… : አርሰናል እና ባርሴሎና በሂደቱ ምን ሊጠቀሙና ምንስ አሉታዊ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ የሚለውን በዝርዝር እንመልከት:-የዝውውሩ ፋይዳ ለፋብሪጋስ :1) ከ “ካምፕ ናው” የድንጋይ ውርውራ ርቀት ላይ “ላ ማሲያ” ተብሎ የሚጠራ ግቢ አለ:: እዛ ዝነኛ ማእከል ውስጥ የወቅቱን አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ጨምሮ አለማችን ላይ አንቱ የተባሉ ተጭዋቾች ገና ለጋ ሳሉ ባርሴሎናዊ ፉትቦል ጥበብን ቀስመዋል:: የአርሰናል አንበልና የፉትቦል አርቲስቱ ፍራንሴስክ ፍሪጋስም የዚህ አካዳሚ ውጤት ከመሆኑም በላይ class of ’87 ተብሎ የሚታወቀው ግሩፕም ቁልፍ አባል ነበር:: ከ እርሱም በተጨማሪ ይህ ስብስብ እንደ ሊዮ ሜሲ ጄራርድ ፒኬ እና ዘግየት ብሎ የተቀላቀለው ፔድሮ የመሳሰሉትን ያቀፈ እንደነበር ይታወሳል:: ባጭሩ ከነኚህ አብሮ አደግ እኩዮቹ ጋር ድጋሚ አብሮ ለትልቁ ቡድን መጫወት ያጓጓል:: በተጨማሪም ሴስክ ካታላን መሆኑን አንርሳ::2) የወቅቱ የባርሳ ቡድን አጨዋወታቸው ብቻ ሳይሆን እግረመንገዳቸውንም እያስመዘገቡዋቸው ያሉት ሪከርዶች ምናልባት የምንግዜውም ምርጥ ቲም ሊያስብላቸው የሚችል አይነት ነው:: በሁለት የውድድር ዘመን ብቻ 7 ዋንጫ እንዲሁም ዘንድሮ 99 ነጥቦችን ያከማቹበት የላሊጋ ድልን መጥቀሱ በቂ ይሆናል:: ታድያ ፋብሪጋስፋ ታሪክ በሌሎች ሲሰራ ራቅ ብሎ ከማየት የዚህ ወርቃማ ትውልድ አካል መሆንን ቢሻ ይፈረድበታልን?3) ጓደኞቹ አየሩ ምግቡ (ባጠቃላይ የካታሉኛ ባህል) ናፍቆት እንቅልፍ ቢነሳው አይግረመን:: በተደጋጋሚ እንደታየው ፋብሪጋስ ባገኛቸው የእረፍት አጋጣሚዎች ወሚወዳት ባርሴሎና እየሄደ ያሳልፋል:: የቡድኑን ጨዋታዎችንም “ካምፕ ናው” ላይ እየተገኘ ይከታተላል:: ለንደን አብዛኛውን ግዜ ጨፍጋጋ ናት:: ባርሴሎና ደሞ ፍንትው ያለች:: ይህች ባህር ደጅ ላይ የተንጣለለች ከተማ ተስማሚ አየሯና ሞቅ ያለው ህይወቷ እንኳን ልጇን ቀርቶ መጤውንም ያከንፋል::4) ከምንም በላይ የአንድን ተጭዋች የጨዋታ ዘመን ምሉእ የሚያደርገው ያስመዘገባቸው ድሎች ናቸው:: ይህ ጉዳይ ፋብሪጋስን ሳያሳስበው አልቀረም::አሁን አሁን በማያልቅ የሽግግር ወቅት ላይ ያሉ የሚመስሉት አርሰናሎች ለመጨረሻ ግዜ የዋንጫን ጣእም የቀመሱት በ2005 የእግርኳስ ማህበሩን ዋንጫ ያሸነፉ ግዜ ነበር:: በ ካርዲፉ ሚሊንየም ስቴድየም ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ጨዋታውን ከጀመሩት 11 ተሰላፊዎች መሀከል በቡድኑ ውስጥ አሁን የቀረው የዛኔው የ 18 አመት ታዳጊ ፋብሪጋስ ብቻ ነው:: ( ግብ ጠባቂው አልሙኛ ሶል ካምቤል እና ሮበን ቫን ፐርሲ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ነበሩ):: ከአለማችን ላይ ካሉ ልሂቅ አማካዮች አንዱ ሆኖ ሳለ አምስት አመት ሙሉ እንዲህ ያለድል ከርሞ አሁን ወደዋንጫ ጎተራዎቹ ባርሳ ቤት ልቡ ቢከጅል አይኑም ቢማትር ከጥፋት የሚቆጥርበት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም::ፋብሪጋስ ቢሄድ ምን ይጎዳል?1) ከአርሰናል ወደባርሳ የተጓዙ ሁሉም ማለት ይቻላል አልተሳካላቸውም:: ምናልባት ትዬሪ ኦንሪ ህልሙ የነበረውን የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ማሳካቱ ካልተጠቀሰ በስተቀር ከአንድ ሲዝን ያለፈ አመርቂ ነገር አላሳየንም:: እርግጥ የእድሜና የ አሰላለፍ መወሳሰብ ጉዳዮች እንዳነበሩ አይታበልም:: የ ማርክ ኦቨርማርስ ኢማኑኤል ፐቲ እና አሌክሳንደር ህለብ ተሞክሮ ግን “ማሪኝ” አርሰናል አስብሏቸዋል:: ሶስቱም ተጭዋቾች አርሰናልን መልቀቃቸው የስህተት ውሳኔ መሆኑ በግልጽ ተናግረውታል:: ፋብሪጋስስ ምን ይጠብቀው ይሆን?
2) ከሁሉም አነጋጋሪው የታክቲክና የቡድን ሽግሽጉ ምን ይመስላል የሚለው ይሆናል::
ፋብሪጋስ ተመራጩ ቦታው ላይ እማይጋፋው ባለችሎታ ተጭዋች አለ – ቻቢ!
አተገባበራቸው ይለያይ እንጂ ሁለቱም በባህሪያቸው የጨዋታን ትርታ መቆጣጠር ይወዳሉ:: ለአሁኑ ቻቢ የሚድፊልዱ ንጉስ ነው:: ፋብሪጋስም ለአርሰናል ዘንድሮን እንዳደረገው ለፊት አጥቂው ቀረብ ብሎ ያማካይ አጥቂነትን ሚና ሊጫወት ይችላል:: ይህ ማለት ባላቂው ሲዝን አሰልጣኙ አብዝቶ የተጠቀመው የ 4-3-3 አሰላለፍ በወረቀት ላይ እንዳለ ይሆንና በተግባር ግን ቡድኑ በአንድ አጥቂ እና በአንድ ያዥ አማካይ (holding midfielder) ብቻ ይጫወታል:: ኢንዬስታን ከግራ ሜሲ ከቀኝ ክንፍ የፊት ጫፉ ላይ ደግሞ ዳቪድ ቪያ ወይንም ዝላታን ኢብራሂሞቪች ሆነው ባለሶስትዮሹን የጥቃት መስመር ይሞሉታል:: እነ ፔድሮ, ኦንሪ እና ቦያን ኪርኪችም ለቦታቸው የዋዛ ተፎካካሪ አይሆኑም:: (ይህ ከላይ የተዘረዘረው የ 4-3-3 ፎርሜሽንን ተግባራዊ ያደርጋሉ በሚለው ታሳቢነት ነው::)
ኢንዬስታ ምናልባት ከቻቢ ጎን ቦታውን አስከብሮ ፋብሪጋስ ወደ ግራ እንዲያዘነብል ሊገፋ ይችላል::
አሰልጣኝ ጋርዲዮላ እስካሁን በአመርቂ ሁኔታ የሰራለትን ታክቲክ አፍርሶ አዲስ ነገር ለመሞከር ምን ያህል እንደሚደፍር ለመገመት ያስቸግራል:: ከሞከረስ ‘ይሳካለታል ወይ’? ብሎም መጠየቅ ተገቢ ነው:: ፋብሪጋስም ሊፈጠር በሚችለው የለውጥ ሽግሽግ ሰለባ ላይሆን ምንም ማረጋገጫ የለም::
3) ከ 16 አመት ታዳጊነት አንስቶ እስከቡድን አምበልነት የበቃበትን ቡድን ትቶ መሄድ ለፋብሪጋስ ቀላል አይሆንም:: በሰባራ እግሩ ፍጹም ቅጣት ምት እስከመምታት ያደረሰው የአርሰናል ፍቅር እንደዋዛ አይወጣለትም:: አርሰናል ቤት እንደማንም አይደለም:: ልዩ የቤተሰብ ቡድን ነው:: ተጭዋቾች አሰልጣኝ ቬንገርን በልዩ ፍቅር ነው የሚወዱት:: የሰውየው ውለታን አውርተውት አይጠግቡም:: የሰር አሌክስ ፈርግሰን ፍቅር ከአስፈላጊ ቁንጥጫ ጋ ሲሆን የቬንገር ደግሞ እንደሚሳሳ አባት ከእንክብካቤ ጋር ነው:: ይሄ ሁሉ ስፔን ምድር ላይ አይኖርም::
4) እንግሊዛውያን ደጋፊዎች ከሚታወቁባቸው በርካታ ባህርያቶች መካከል አንዱ ታማኝ ፍቅራቸው ነው:: ቆይታው አጭር ይሁን ረጅም አንድ ተጨዋች ልባቸው ከገባ ለዘላለም ይዘክሩታል:: ብራዚላዊውን ጁኒንዮ በሚድልስብሮ ሪቨርሳይድ ስቴድየም “አምላክ” እያሉ አሁንም ያሞካሹታል:: ካንቶናንም መጥቀስ ይቻላል:: ፋብሪጋስ በስካሁኑ የሰሜን ለንደን ቆይታው ለቡድኑ የከፈለው መስዋእትነት የደጋፊውን ፍቅር መግዛት ችሏል::
የስፔን ፉትቦል ባህል ግን እጅጉን ይለያል :: ሊያደንቁም ሊያንቋሽሹም ችኩል ናቸው:: ወቅታዊ እንቅስቃሴና ውጤት ከምንም በላይ ትኩረት ይሰጣቸዋል:: እንደዚያ ያስፈነደቃቸው ተአምረኛውን ሮናልዲኞ ፊታቸው ሊያዞሩበት ጥቂት ወራቶች ብቻ በቂ ነበሩ:: ( እርግጥ ሮናልዲኞ ከሜዳ ውጭ የሚያረጋቸው ነገሮች ትክክል አልነበሩም)::
ስለዚህ ፋብሪጋስ ኤምሬትስ ስታድየምን ለቆ ሲሄድ ጥሎ የሚሄደው ይህ ከደጋፊው አለገደብ የሚለገሰው ” unconditional love”ን ጭምር ነው::
በኑ ካምፕ የሚጠብቀውን ማንም አያውቅም::
ለአርሰናል ጥቅምና ጉዳቱ :
ጉልህ ጥቅሙ ያው ዳጎስ ያለ ገንዘብ ያገኙበታል:: ከፈለጉ ክለቡ ያለበትን እዳ ለመክፈያ ያውሉታል:: ካሻቸው ደግሞ በከፊሉ የፋብሪጋስን ተተኪ የማስፈረም እድልን ይፈጥርላቸዋል (የፈረንሳዩ ጨዋታ አቀጣጣይ ዮሀን ጉርኩፍን በጎን እያነጋገሩ እንደሆነ እየተሰማ ነው):: ጉዳቱን ያየን እንደሆነ አርሰናል የሚያጣው አውራ ተጭዋቹን ነው:: ይህ በራሱ ቡድኑን 2 እርምጃ የሗሊዮሽ የመጎተት ሀይል አለው:: የራቃቸውን ድል ባጭር ግዜ ውስጥ ማስመዝገብ ከፈለጉ ፋብሪጋስና ቫንፐርሲ የግድ የዚህ ቡድን አካል መሆን አለባቸው:: አለበለዝያ እንደገና ግንባታ ሌላ ረጅም ዋንጫ አልባ ጉዞ!
ዝውውሩ ከተሳካ አርሰናልን ለድል ከሚፋለም ቡድንነቱ ይልቅ ለሌሎች መጋቢ ቡድን አድርጎ የመመልከት አዝማምያው ሊያይል ይችላል:: ይህ ደሞ በቀሩት ተጭዋቾች ዘንድ ያልተፈለገ ስነልቦናዊ ጫናን ያሳድራል::
ለባርሳ ጥቅምና ጉዳቱ :
በችሎታ የተትረፈረፉት ባርሳዎች ባላቸው ስብስብ ላይ ፋብሪጋስን ካከሉበት ምን አይነት ቡድን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰቡ ራሱ ይከብዳል:: ማንስ ያቆማቸዋል? ሜሲ በአንድ ወቅት ” ይህን የባርሳ ቡድን ካለበት ሊያሻሽሉት ከሚችሉ ጥቂት ተጭዋቾች መካከል አንዱ ፋብሪጋስ ነው” ብሎ የልጁን መቀላቀል በጉጉት እንደሚጠብቀው ተናግሯል:: በተጨማሪም አመራሮቹ ሁሌ ለሚተጉለት የካታሉኛ ግዛት መመክያ ምልክትነት የፋብሪጋስ ወደ አሳዳጊው ክለብ መመለስ አላማቸውን ያጠናክረዋል::
ጉዳቱ ተብሎ የሚሰጋው የባርሴሎና ጋላክቲኮ አዝማምያ ነው:: ከዋክብትን የማሰባሰብ ሱስ በስተመጨረሻ ሪያል ማድሪድን ለውድቀት እንዳበቃው ማንም ያስታውሳል:: ባላቸው ከበቂ በላይ ግሩም ስብስብ ላይ የነፋብሪጋስ መታከል ለአያያዝ አስቸግሮ እንደ ተቀናቃናቸው ሁሉ ፍርክስክሱ እንዳይወጣ የደጋፊው ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ጸሎትም ያሻል::



Hi jegnaw minew tefah
i think it is good for him
it is not good to him b/c he can not compit with barcelona’s pleayer